የጋብቻና የቤተሰብ አገልግሎት
ቤተ ክርስቲያናችን እግዚአብሔር ከሰጣት ትልቅ ሸክም መካከል አንዱ ሲሆን ይህ ሸክም በራዕይ ተቀባዮቹ በመጋቢ ብርሃን ጫነና በመጋቢ ሜርሲ መስፍን ልብ ውሰጥ የሚቀጣጠልና ለረጅም ዓመት ሲሰሩበት የነበረ የአገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በጋብቻ ዙርያ የተለያዩ ትምህርት፣ ምክርና ስልጠና በየጊዜው እያዘጋጀች በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ የምትሰጥና አሁንም እየሰጠች ያለች ናት፡፡ በተለይም በትዳራቸው ችግር የገጠማቸውን ቤተሰቦች በቤተ ክርስቲያን እና ባሉበት ስፍራ በመሔድ የምክርና የማስተካከል ሥራዎችን ትሰራለች፡፡
በዚህ ዘርፍ መጽሐፍ በመጻፍ፣ በቴሌቪዥን ስርጭት ተከታታይ ትምህርትና በተለያዩ ስፍራዎችና ከተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት ጋር በመቀናጀት ትምህርትና ስልጠና በመስጠት ለብዙ ትዳሮች መፈወስ ምክንያት ሆናለች። ከዚህ ቀደም ትዳራችንን እንዴት እንፈውሰው? የሚል መጽሐፍ በመጻፍ ለንባብ ያቀረበች ሲሆን በአሁኑ ወቅት ይህንኑ መጽሐፍ በኦሮሚኛ በመተርጎምና የተለያዩ አካባቢዎችን ለመድረስ እየተጋች ነው፡፡ እንዲሁም የዚህን መጽሐፍ ክፍል ሁለት እትም በቅርብ ጊዜ ይዛ ትቀርባለች፡፡
በዚህ የአገልግሎት ክፍል ባለ ትዳሮችን ብቻ ሳይሆን በተለይም ለትዳር ትልቁ ካንሰር የሆነው ከጋብቻ በፊት ስለ ትዳር እወቀት ማጣት በመሆኑ መታወቅ ያለባቸውን መሰረታዊ እውቀትን እንዲጨብጡ ትዳር የሌላቸውንና ለማግባት ለተዘጋጁ ወገኖች መሰረታዊ የሆኑ ትምህርቶችን በሰፊው ታስተምራለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ አገልግሎት በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችንም የሚሰጥ በመሆኑ መገልገል የሚፈልግ ወገናችን ይህንን አገልግሎት በነጻ ማግኘት እንደሚችል ስንገልጽ በደስታ ነው፡፡
እንዲሁም የጋብቻ ትምህርት ለሚፈልጉ ሁሉ ተከታታይ ትምህርት በመስጠት የማማከር እውቀት ለሚፈልጉም ሆነ ለራሳቸው እውቀት ማግኘት ለሚፈልጉ ስልጠናዎችን እየሰጠን እናስመርቃለን፡፡ ይህንን አሰራር በሃገራችን ብቻ ሳይሆን አሜሪካ ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ስፍራዎች በተደጋጋሚ ተግብረነዋል፡፡ ሥራውንም በአሁኑ ወቅት መሪ አገልጋዮቿ ብቻ ሳይሆኑ በዚህ ዘርፍ ሰልጥነው ክህሎት ያዳበሩ አገልጋዮች እየሰሩት ይገኛሉ፡፡