የእግዚአብሔር ፍጹም ሙላት አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን አጀማመርና እድገት
የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ሆኖ የእግዚአብሔር ፍጹም ሙላት አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን የት፣ መቼ እና አንዴት ተመስርታ ዛሬ ያለችበት ደረጃ ደረሰች የሚለውን ስንመለከት እግዚአብሔር የመጀመርያ ራዕይ ተቀባይ ለሆኑት በመጋቢ ብርሃን ጫነና በመጋቢ ሜርሲ መስፍን ልብ በአሰቀመጠው ራዕይ በኤፌ. 3፡18-19 ላይ በሚገኘው “ወደ እግዚአብሔር ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ” በሚለው የእግዚአብሔር ቃል መሰረት ተቋቋመች። የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ የሰውን ልጅ ከተለያዩ ከሰይጣን ፣ ከዓለም እና ከሰው ሙላት በማውጣት ወደ እግዚአብሔር ፍጹም ሙላት ለማምጣት በታላቅ እምነት የምትቀጣጠልና የተለያዩ የእግዚአብሔርን ሥራ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት በመስራት ላይ ያለች ቤተ ከርስቲያን ናት፡፡
በ1998 ዓ.ም (2005) በአዲስ አበባ ከተማ ቄራ መብራት ሃይል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቁጥራቸው ከስምንት በማይበልጡ እግዚአብሔርን በሚወዱ ግለሰቦች በመጀመሪያ ራዕይ ተቀባይ በመጋቢ ብርሃን ጫነ መኖሪያ ቤት በህብረት ደረጃ የተቋቋመች ስትሆን ከጌታ ከተቀበለችው ራዕይ በስተቀር ምንም መተዳደሪያ ገንዘብም ሆነ የማምለኪያ ሥፍራ አልነበራትም፡፡ በዚህን ጊዜ ለማምለኪያ ትጠቀምበት የነበረው የመጋቢዎቹ መኖሪያ ቤት በመጥበቡ ጦር ኃይሎች አካባቢ ወደ ነበረው መጋቢ በቀለ ላቀው ቤት በመዘዋወር ለሁለት ዓመት ገደማ በጸሎትና በማምለክ ቆየች። ከዚህ በኋላ በአካባቢው ያለው የመኖርያ ቤት አሰራርና የህዝብ አሰፋፈር ቤተ ክርስቲያንን ለማስፋፋትና ለማሳደግ አመቺ ባለመሆኑ እንደገና ቀድሞ ወደ ተመሰረተችበት ቄራ መብራት ኃይል በመመለስ አምልኮዋን ቀጥላለች። በእግዚአብሔር ምሪትም ወደ ላፍቶ አካባቢ ወረዳ አስራ ሁለት በመቀየር ከአንድ መቶ ካሬ ሜ. የማይበልጥ የማምለኪያ ስፍራ ያለውን ግቢ በ1200.00 ብር በመከራየት አገልግሎቷን አንቀሳቀሰች።፡፡
የእግዚአብሔር ፍጹም ሙላት አለም አቀፍ ቤ/ክን የገጠማት ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ እንደሚታወቀው በክርስቶስ ደም በተዋጀች ቤተክርስቲያን ላይ ይደርስ ከነበረው ስቃይ፣ ስደትና መከራ ጋር ሲታይ ሚዛን የሚደፋ ባይሆንም የክርስቶስ ተምሳሌት የሆነች ቤተክርስቲያንን ማሳደድና ማፍረስ ጽድቅ በሚመስላቸው አካላት በሰማያዊ ድንኳን ተወጥራ በተገነባችው በዚህች አነስተኛ የማምለኪያ ስፍራ ላይ ብዙ ወጅብ ተነስቶ እንድትፈርስ ተደርጋ ነበር፡፡ በምናመልክበት ስፍራ ድንዃን ማድረግን በመከልከል በአምልኮ ወቅት ብቻ ድንኳንዋን እየወጠረች አምልኮው ሲያልቅ ድንኳንዋን እንድትጠቀልልና እንድታነሳ በተወሰነባት ውሳኔ መሰረት ይህንኑ በመተግበር ለስምንት ዓመታት በዚሁ ዓይነት ሁኔታ ለማምለክ ተገዳ ነበር፡፡
ከዚህም ተግዳሮት ባሻገር የወንበር ችግር እና የፈሳሽ ማሳተላለፊያ ቦይ ያልተሰራለት ግቢ በመሆኑ በክረምት ወቅት የዝናብ ውሃ በግቢው ውስጥ ስለሚከማች ውሃውን የማውጣት ሥራ ይሰራ የነበረው በአባላቱ ጉልበት
በመሆኑና የስራው አድካሚነት ተስፋ የሚያስቆርጥ ነበር፡፡ እንዲሁም በዝናብ ወቅት በድንኳኑ ላይ የሚከማቸው ውኃ በተደጋጋሚ በሚያመልከው ምዕመን ላይ በመፍሰስ እና በበጋ ወቅት ደግሞ ወንበር ላይ ይከማች የነበረው አቧራ በየአምልኮው እለት ማጽዳትና በየአምልኮው ጊዜ የሚወረወር የድንጋይ ናዳን መቋቋም የዚህች ቤተ ክርስቲያን የቅርብ ጊዜ ትዝታዋና ተግዳ ሮቷ ነበር፡፡
የጌታ መልካም ፈቃድ በመሆኑ ዛሬ በለቡ መብራት ኃይል አደባባይ በሳሙኤል ሕንጻ ሶስተኛ ፎቅ በተንጣለለ አዳራሽ የለቡ ቅርንጫፍ አጥቢያ ቤተክርስቲያኗን ስትመሰረትና ሥፍራ ስትቀይር አብረዋት ከነበሩት አብሮ ሰራተኞች ብዙዎቹ ሁለት ኪሎ ሜትርን እንደ ርቀት በመቁጠር ቀርተው ነበር። ትልቅ አዳራሽን በጥቂት ሰዎችና በውድ ክፍያ ተከራይተን ገብተን አምላካችን ታማኝ በመሆኑ አሁን እስከደረስንበት ደረጃ አሰፋን፡፡
ባለፉት አመታት ሁሉ ቤተክርስቲያኒቷ እያደገች እና ራዕይዋን እያሳካች አሁን ባለችበት ሁኔታ ትገኛለች። እግዚአብሔር ብቻ ማድረግ የሚችላቸውን ነገሮች በመካከላችን ሲሆኑ ማየት የቻልን እድለኞች ነን። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ዳግም የተወለዱበት፣ ህይወት የተቀየረበት፣ ጋብቻዎች የታደሱበት፣ የቆሰሉ ቤቶችና ህይወቶች የተፈወሱበት፣ የተሰበሩ ልቦች የተጠገኑበት ቦታ ነው። እግዚአብሔር ባዘጋጀልን መድረኮች እና በከፈተልን ደጅ ሁሉ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ፣ አቃተኝ ሳንል በታላቅ ቅንዓት በወንጌል ያልተደረሱትን ሰዎች ህይወት ሰጪ በሆነው ወንጌል ለማዳረስ በከተማችን ብሎም እስከ አለም ዳርቻ ለመነቀሳቀስ የተዘጋጀን ሰዎች ነን። የወንጌል እውነትን በመስበክ፣ በማስተማር እና በመተግበር ፈጠራ በተሞላው መልኩ ጊዜ የማይሽረውን የክርስቶስን መንግስት ወንጌል ግልፅና አዲስ (Fresh) በሆነ መንገድ የምናቀርብበት ቤተክርስቲያን ነው።
የጌታ መልካም ፈቃድ ሆነና በመቀጠልም በእግዚአብሔር ቃል መሰረት ቤተክርስቲያንን በከተማ፣ በመንደር እና በገጠር መመስረት የሚለውን መርህ በመከተል በአሁኑ ወቅት በለቡ፣ በአለም ገና፣ በሃና ማርያም፣ በቃሊቲ፣ በቦሌ ቡልቡላ፣ በደብረ ዘይት፣ በገርጂ፣ በወለቴ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ውጪ በአሜሪካ በአትላንታና በላንካስተር ከተሞች ላይ አጥቢያዎችን የከፈተችና በመክፈት ላይ የምትገኝ ናት። ይህም አሰራር እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኗ ከሰጣት አንድ ሺ ቤተ ክርስቲያንን በአስር ዓመት የመትከል ራዕይ መሠረት ነው፡፡